ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ተናገረ ማቴ. 24:1-51

ክርስቶስ ስለ ቤተ መቅደሱ ሙሉ በሙሉ መፈራረስ በተነበየበት ወቅት፥ ደቀ መዛሙርቱ በድንጋጤ መራዳቸው አይጠራጠርም። ቤተ መቅደሱ በጥንቱ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ ሕንጻዎች አንዱ ነበር። እግዚአብሔርም የሚመለክበት ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር እንዴት ይህ ቤተ መቅደስ እንዲፈርስ ይፈቅዳል? ይህ የሚሆነውስ መቼ ነው? ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ክስተቶች እንዲያብራራላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ጥያቄያቸውን የመለሰው በቅርቡ የሚፈጸመውን የቤተ መቅደስ መውደም ገና ከሚሆነው የእርሱ ምጽአት ጋር በማጣመር ነበር። (ስለ ምጽአቱ ከተነበየ አሁን 2000 ዓመታት አልፎታል።) ትንቢትን መተርጎም በጣም አስቸጋሪ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ በአነስተኛ የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ (with little time frame) አንዳንድ ትንቢት በፍጥነት ሊፈጽሙ ሲችሉ፥ ሌሎች ብዙ ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸው ነው። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ አንድ ትንቢት ሁለት ወይም ከዚያ የበለጡ ፍጻሜዎች ያሉት መሆኑ ትንቢትን የበለጠ ያወሳስበዋል።

ምሑራን በእነዚህ ትንቢቶች አተረጓጎም ላይ የሚከራከሩ ሲሆን፥ አንዳንዶች ይህ ሁሉ በ 70 ዓ.ም. ሮማውያን ቤተ መቅደሱን ባፈራረሱበት ጊዜ እንደ ተፈጸመ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችበት ጊዜ ከትንቢቶቹ ብዙዎቹ በከፊል ቢፈጸሙም፥ አብዛኛዎቹ ግን በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ ትንቢቶች መቼና እንዴት ይፈጸማሉ? በሚሉ ዝርዝር አሳቦች ላይ ብዙ ውዝግቦች ታይተዋል። እነዚህን ትንቢቶች የምንረዳበት መንገድ በቀደሚነት እስራኤል ወደፊት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚኖራት ድርሻ ባለን ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ትንቢቱ እስኪፈጸም ድረስ መረዳቱ አዳጋች ስለሆነ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኛ የተለየ አቋም ለሚይዙት የጥላቻ ስሜት ሊኖረን አይገባም። ከክርስቶስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት፥ እስከ ሞቱና ትንሣኤው ድረስ ትንቢትን እንዴት እንደ ፈጸመ ለመገንዘብ ከተቸገሩ፥ እኛም ትንቢቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት መቼና እንዴት እንደሚፈጸሙ ለማወቅ መቸገራችን የማይቀር ነው።

ክርስቶስ ትንቢቶቹ የሚፈጸሙበትን ትክክለኛ የጊዜ ማእቀፍ ወሰን ሳይሰጥ፥ ለደቀ መዛሙርቱ አመልካች «ምልክቶችን» ብቻ ሰጥቷቸዋል። ከምልክቶቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-

ሀ. ብዙ የሐሰት መሢሖች ይነሣሉ። በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም ከመደምሰሷ በፊት ብዙ ሰዎች የተስፋ ቃል የተሰጣቸው መሢሖች መሆናቸውን እየገለጹ ለሥልጣን ቢሯሯጡም፥ ከሮማውያን እጅ አላመለጡም። ክርስቶስ ከመመለሱ በፊትም ብዙዎች ይህን ሥልጣን ለራሳቸው ለማድረግ ይሽቀዳደማሉ። ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ «ሐሳዊ – መሢሕ» ወይም «የዐመፅ ሰው» እያለ የሚጠራውን ሐሰተኛ የራሷ መሢሕ አድርጋ ትቀበላለች ራእይ 12፤ 2ኛ ተሰ. 2፡3-12)።

ለ. ጦርነት፥ የጦርነት ወሬ፥ አብዮትና የቤተሰብ ጠብ ይበዛል።

ሐ. በክርስቶስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት ይጨምራል። ዓለም ክርስቲያኖችን መታገሥ ተስኖት ያሳድዳቸዋል፥ ይገድላቸዋል።

መ. የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እምነታቸውን ይክዳሉ።

ሠ. ብዙ ሰዎችን የሚያታልሉ በርካታ የሐሰት አስተማሪዎችና ነቢያት ይነሣሉ። እነዚህ ሐሰተኞች ተአምራትን ሳይቀር ሊሠሩ ይችላሉ (ማቴ. 24፡24)።

ረ. የዓለማውያን ክፋት የሚጨምር ሲሆን፥ ብዙ ክርስቲያኖች ለክርስቶስና ለወንጌሉ የነበራቸው ፍቅር ይቀዘቅዛል።

ሰ. ወንጌሉ በሁሉም አገር ለሚገኙ ጎሳዎች ይሰበካል። ክርስቶስ ይህ ከመጨረሻው ዘመን ዐበይት መረጃዎች አንዱ እንደሆነ ገልጾአል። በአሁኑ ዘመን በዓለም ለሁሉም ጎሳዎች ማለት ይቻላል ወንጌል ተሰብኮ የተወሰኑ ክርስቲያኖች አምነዋል። ስለሆነም፥ ይህ ትንቢት በዘመናችን ሊፈጸም እንደ ቀረበ ልንመለከት እንችላለን።)

ሸ. «ች» የተባለ፥ ሃይማኖታዊ ርኩሰት ይከሰታል። አብዛኞቹ ምሑራን ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችና የሮም ወታደሮች ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብተው ባወደሙት ጊዜ፥ ይህ ትንቢት መጀመሪያ እንደ ተፈጸመ ያምናሉ። (እንዲሁም ዳንኤል ስለዚህ ጉዳይ የሰጠው ትንቢት በ168 ዓ.ዓ አንቲዮስስ ኤጲፋነስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያው ላይ አሳማ በሠዋ ጊዜ፥ በቀዳሚነት እንደ ተፈጸመ ይናገራሉ።) አንዳንድ ምሑራን፥ ደግሞ ይህ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ኣይሁዶች ሌላ ቤተ መቅደስ እንደሚገነቡና ሐሳዊ መሢሕ እንደሚያረክሰው የሚያመለክት ነው ይላሉ።

ቀ. ክርስቶስ ሕዝቡ ከአደጋው እንዲሸሽ አዝዟል። ማቴዎስ ይህን መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ፥ ብዙም ሳይቆይ በኢየሩሳሌም ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህን ጊዜ ክርስቲያን የሆኑ አይሁዶች ምን ማድረግ ነበረባቸው? በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ከሌሎች ኣይሁዶች ጋር ይሙቱ ወይስ ይሽሹ? አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ ሸሽተው ሕይወታቸውን እንዲያተርፉ እንዳዘዛቸው ያምናሉ። ይህ የመጨረሻዎቹን ትግሎች ፍጥነት ያሳያል።  

በ. የመጨረሻው ዘመን አስፈሪ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ጊዜውን ባይገድብ ኖሮ፥ በምድር ላይ አንድም ሰው አይድንም ነበር። «ምርጦቹ» በእነዚህ ቀውጢ ቀናት ውስጥ ስለሚኖሩ እግዚአብሔር ጊዜውን ይገድበዋል።

ተ. የክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ድንገተኛና ያልተጠበቀ (እንደ መብረቅ) ይሆናል። ይህም ሆኖ፥ የምጽአቱን መቃረብ የሚያሳዩ በቂ ምልክቶች ይኖራሉ። (በሰማይ የአሞራዎች ማንዣበብ የሞተ ነገር መኖሩን ያመለክታል።) እንዲሁም በበለስ ዛፍ ላይ የሚገኙ ቅጠሎች አንድን ወቅት እንደሚያሳዩ ሁሉ፥ ክርስቶስ የሰጣቸው እነዚህ ምልክቶችም በቅርብ እንደሚመለስ ያሳያሉ።

ቸ. ፀሐይን፥ ጨረቃንና ከዋክብትን የሚያናጋ ታላቅ የዓለም (cosmic) ውድመት ይሆናል።

ኀ. ክርስቶስ በሙሉ ኃይሉና ሥልጣኑ በደመናት ይገለጻል። በዚያን ጊዜ መጀመሪያ ሲመጣ እንደሆነው ሁሉ ሰብአዊነቱ ሳይሆን አምላክነቱ ይገለጣል። በመላእክትና በመለከት ድምፅ ታጅቦ ይመጣል። የሁሉም አገር ሰዎች ክርስቶስን በሚያዩበት ጊዜ ያለቅሳሉ። የሚያለቅሱት በንስሐ ይሁን ስለሚፈረድባቸው የምናውቀው ነገር የለም።

ነ. የተመረጡት ከዓለም ተለይተው ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ክርስቶስ «ይህ ሁሉ እስኪሆን ይህ ትውልድ አያልፍም» (ማቴ. 24፡34) ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ አነጋግሯል። በኣጠቃላይ አራት ዐበይት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በኣንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌም በሮማውያን እንደምትወድም የሚናገሩ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ መግለጹ ነው የሚሉ አሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የተጠቀሰው ትውልድ የክርስቶስን ዳግም ምጽኣት የሚያሳዩ ምልክቶች በሚጀምሩበት ጊዜ የሚኖረው እንደሆነ ያስባሉ። ስለሆነም፥ ምልክቶቹ በተጀመሩ 40 ዓመታት ውስጥ ክርስቶስ ይመለሳል ብለው ያስባሉ። ሦስተኛ፥ «ትውልድ» የሚለው ቃል «ዘር» ተብሎ ሊተረጎም ስለሚችል፥ ክርስቶስ እርሱ ከመመለሱ በፊት የአይሁድ ዘር እንደማይጠፋ መግለጹ ነው ይላሉ። አራተኛ፥ አንዳንዶች የሌሎችን አመለካከቶች ውህድ አድርገው ያዩታል። የክርስቶስ ትንቢቶች የ70 ዓመተ ምሕረቱን የኢየሩሳሌምን መደምሰስና እርሱ የሚመለስበትን የመጨረሻ ዘመን የሚያጠቃልሉ ስለሆኑ፥ ብዙ ደቀ መዛሙርት የኢየሩሳሌምን ውድመት እንደሚመለከቱ ያስተምራሉ። ስለሆነም፥ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ይመለከቱ ዘንድ እግዚአብሔር የአይሁድን ዘር ከጥፋት ይጠብቃል።

ኘ. ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ በርግጠኝነት የሚያውቅ ማንም የለም። ይህ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብለን እንዳንናገር ሊያስጠነቅቀን ይገባል። (በታሪክ ሁሉ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሙከራዎችን አካሂደው መሳሳታቸው ታውቋል። ይህ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውዝግብ ከማስከተሉም በላይ፥ የክርስቲያኖችና የክርስቶስን ስም ያሰድባል።)

ምሑራን ክርስቶስ ስለሚመለስበት ጊዜ እንደማያውቅ በተናገረው አሳብም ላይ ይከራከራሉ። «ክርስቶስ አምላክ ከሆነ፥ እንዴት አያውቅም?» ብለው ይጠይቃሉ። ለዚህ ጥያቄ ቀላል ማብራሪያ ማቅረብ አይቻልም። ምናልባትም ከሁሉም የሚሻለው ማብራሪያ፥ ክርስቶስ በምድር ላይ በሰብአዊ ማንነቱ በነበረበት ጊዜ፥ መለኮታዊ እውቀቱን እንደ ወሰነ የሚያመለክተው አሳብ ይሆናል። ስለሆነም፥ እንደ ሰው አለማወቁን ሊናገር ይችላል። አሁን ግን በምልዐተ መለኮቱ በሚኖርበት ሰማይ የሚመለስበትን ጊዜ ያውቃል።

አ. ክርስቲያኖች ሊያስተውሉት የሚገባው ከሁሉም የላቀው እውነት፥ ምን ጊዜም መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው። ለጉዞ ወጥቶ ባልተጠበቀ ሰዓት እንደሚመጣ ባለሀብት፥ ክርስቶስ በየትኛውም ሰዓት ሊመጣ ይችላል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ እንዳናፍርና ድንገተኛ ሆኖብን እንዳንደናገር፥ በየቀኑ ክርስቶስ ሊመጣ እንደሚችል እያሰብን ልንኖር ይገባል። እርሱ በሚመለስበት ጊዜ በታማኝነት እያገለገልነው ከተገኘን ሽልማቱን እንቀበላለን። ይህ ካልሆነ ግን የከፋ ቅጣት ይጠብቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚመጣ ብናውቅ ኖር፥ እንዴት ኣድርገን የኣስተሳሰባችንና የተግባራችንን ሁኔታ እንለውጥ ነበር? ለ) ይህ ክፍል ክርስቶስ ዛሬ እንደሚመጣ እያሰብን እንድንኖር የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ሐ) አብያተ ክርስቲያኖቻችን ክርስቶስ በእውነት እንደሚመጣ እያሰቡ ቢኖሩ፥ ትኵረታቸውንና ተግባራቸውን እንዴት ይለውጣሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading