ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

ምንም እንኳ ብዙዎቹ የጳውሎስ መልእክቶች የተጻፉባቸውን ቁርጥ ጊዜያት መናገሩ አስቸጋሪ ቢሆንም፥ 1ኛ ቆሮንቶስን የጻፈው በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ኤፌሶን ውስጥ እያገለገለ ሳለ መሆኑ ግልጽ ነው። ጳውሎስ እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ በኤፌሶን እንደሚቆይና ከዚያ በኋላ ቆሮንቶሶችን እንደሚጎበኝ ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 16፡8፥19፣ በተጨማሪም የሐዋ. 19፡10ን አንብቡ።) ይህም የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት የተጻፈው ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከተከለ ከ5 ዓመታት በኋላ በ55 ዓ.ም መሆኑን ያሳያል።

ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የጻፋቸው መልእክቶችና ያደረጋቸው ጉብኝቶች ቅደም ተከተል

ምሁራን ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ባደረጋቸው ጉብኝቶችና በተለይም በጻፋቸው የተለያዩ መልእክቶች ቅደም ተከተል ላይ ይከራከራሉ። ጳውሎስ በኤፌሶን ላይ ባተኮረበት በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወቅት አራት የተለያዩ መልእክቶችን የጻፈ ይመስላል።

በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ አንድ መሠረታዊ የመጀመሪያ መልእክት ሳይጽፍ እንዳልቀረ ብዙ ምሁራን ያምናሉ (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። ይህ መልእክት ጠፍቷል። ጳውሎስ በዚህ የመጀመሪያ መልእክቱ ስለ ግብረገባዊ ንጽሕና ላያስተምር አልቀረም። የቆሮንቶስ ሰዎች ንጹሕ ግብረገባዊ ሕይወት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳያደረጉ አሳስቧቸዋል (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። ክርስቲያኖቹ የጳውሎስን አሳብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ይህ ማለት አምልኮተ ጣዖት ከሚያካሂዱና ግብረገባዊነት የጎደለው የወሲብ ግንኙነት ከሚፈጽሙ ዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግን ያሳያል ብለው አሰቡ። የክርስቲያኖች ከዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግ መልካም ውጤት የሚያስገኝ ነገር አልነበረም። እንደዚያ ከሆነ፥ ለማያምኑ ሰዎች መስክረው ወደ ክርስቶስ የሚመልሷቸው እንዴት ነው? ጳውሎስ የሚናገረው ለክርስቶስ ለመገዛትና የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመከተል ከማይፈልጉ ክርስቲያኖች ጋር ኅብረትን ስላለማድረግ ነበር። ጳውሎስ አማኞችን ወደ ንስሐ ለመምራትና ለመቅጣት በማሰብ እነዚህ ግብረ ገባዊነት የጎደላቸው ክርስቲያኖች ከክርስቲያናዊ ኅብረት እንዲገለሉ ነበር የተናገረው። የዚህም ቅጣት ዓላማ አማኞቹ አፍረው በኃጢአት ከተሞላው አኗኗራቸው እንዲመለሱ ለመርዳት ነበር።

እንደ ቆሮንቶስ ሰዎች ሁሉ፥ ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች በግልጽ ኃጢአት ከሚመላለሱ ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደሚያደርጉ ይቸገራሉ። ኃጢአትን እየፈጸሙ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ወደ መታገሡ እናዘነብላለን። ክርስቲያኖች ካልሆኑና በክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ለመኖር ከሚፈልጉት ክርስቲያኖች ደግሞ ራሳችንን እናገኛለን። ብዙውን ጊዜ ምስክርነታችን ደካማ የሚሆነውና ብዙ ዓለማውያን ወደ ክርስቶስ የማይመጡት ለዚህ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቀዳሚነት ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ብቻ ኅብረት ለማድረግ ክርስቲያኖች (በተለይም የክርስቲያኖች ልጆች) ዝንባሌ ማሳየታቸውን እንዴት እንደታዘብህ ግለጽ። ለ) ይህ በቤተ ከርስቲያን ላይ ያስከተለው አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው?

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ሊጎበኙት ከመጡት የቆሮንቶስ አማኞች በመካከላቸው ስለነበረው ክፍፍል ከሰማና ቤተ ክርስቲያኒቱ የተወሰኑ ጥያቄዎችን በማንሣት የላከችለትን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ፥ ሁለተኛውን መልእክት ጻፈ። ይህም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተካትቶ የምናገኘው የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ነው። ጳውሎስ አጵሎስ ወደ ቆርንቶስ ተመልሶ ችግሮችን እንዲፈታ ቢጠይቀውም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም (1ኛ ቆሮ. 16፡12)። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በሌሎች ሰዎች፥ ምናልባትም ሊጎበኙት በመጡት የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አማካኝነት ደብዳቤውን ላከላቸው።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ በኋላ አንዳንድ ችግሮች እርሱ በፈለገበት መንገድ ሳይሄዱለት የቀሩ ይመስላል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። ጳውሎስ ይህንን ጉብኝት «የሥቃይ ጉብኝት» ብሎታል (2ኛ ቆሮ. 2፡1)። ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ፥ «የኃዘን ደብዳቤ» የተባለ ሌላ መልእክት ጽፎ በቲቶ በኩል ሰደደ (2ኛ ቆሮ. 2፡4፤ 7፡8-9)። (አንዳንድ ምሁራን ይህ የ1ኛ ቆሮንቶስን መልእክት ያመለክታል ይላሉ። ሌሎች ግን በዚህ መልእክት ውስጥ ብዙ ኃዘን እንደሌለ በመግለጽ፥ ጳውሎስ አሁን በእጃችን ስለሌለ መልእክት እየተናገረ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።)

አራተኛ፥ ጳውሎስ የኤፌሶን አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቆሮንቶስና ኢየሩሳሌም አመራ። ይህንንም ያደረገው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የመሠረታቸውን አብያተ ክርስቲያናት በእግር እየተጓዘ በመጎብኘት በመቄዶንያ በኩል በማለፍ ነበር። በተጨማሪም፥ አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ድሆች ክርስቲያኖች እንዲሰጥ ያዋጡትን ገንዘብ ሰብስቧል። ጳውሎስ በመቄዶንያ ሳለ፥ ቲቶ ከቆሮንቶስ ተመልሶ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መለወጥ ገለጸለት (2ኛ ቆሮ. 7፡5-7)። ጳውሎስም በአመስጋኝነት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የሚገኘውን የሁለተኛ ቆሮንቶስን መልእክት ጻፈ።

ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ደርሶ በጋውን (3 ወራት ያህል) እዚያው አሳለፈ። ከዚያም የአሕዛብ ክርስቲያኖች ለአይሁድ ክርስቲያኖች ያዋጡትን ገንዘብ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading